በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተፃፈላቸው ብዙ መፈንቅለ መንግስቶች ተደርገዋል። የሁለት፣ ወይንም የሶስቱን ብቻ በታሪክ እናገኘዋለን።
~በቀዳሚነት ተፅፎ የምናገኘው የ1953 ዓም መፈንቅለ መንግስትን ነው። ይህ መፈንቅለ መንግስት ስርዓቱ ኮትኩቶ ባሳደጋቸው፣ ለንጉሱ ሰግደው፣ የንጉሱን ትዕዛዝ የቅዱስ መፅሐፍ ቃል ያህል ሲያከብሩ የኖሩ የሞከሩት ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ ያደጉት መኮንኖች የሕዝብ ብሶት፣ የስርዓቱ ድክመቶችና ሌሎች ለውጦችን ሲገነዘቡ ያደርጉታል ተብለው የማይታሰበውን አድርገውታል።
~ሌላኛው በታሪክ ውስጥ የተሻለ ሰነዶች ያሉት የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግስት ነው። በ1953 ዓም ቃላቸው የመፅሐፍ ቃል አድርገው የሚወስዱት፣ “ጃንሆን” እያሉ መንበራቸው ላይ እንደተነሱት ሁሉ፣ በአንድ ወቅት ኮ/ል መንግስቱን በማርክሲስም ሽፋን ንጉስ አድርገው ይቆጥሩ የነበሩ፣ ከጓድ መንግስቱ አመራር ሲሉ የነበሩ መኮንኖች የፈፀሙት ነው። ልዩነቱ በአጤው ዘመን መለኮታዊ፣ በደርግ ወቅት ርዮትዓለማዊ መሆኑ እንጅ ሁለቱን መሪዎች መኮንኖቹ ለማምለክ ደርሰዋል።
~ሶስተኛና በክስ ደረጃ ተፅፎ የሚገኘው በ2000 ዓም ተደረገ የተባለው ሲሆን ይህን ሙከራ አደረጉ የተባሉትም ከሁለቱ ስርዓቶች የሚለዩበት አውዶች ቢኖሩም፣ በስርዓቱ ያደጉ “ታጋዮች” አደረጉት የተባለው ነው። የዚህኛው ልዩነት ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ መገፋቱን በዚሁ ማንነት ላይ የመጣ መሆኑ ነው።
~ብዙውን ጊዜ የማይወራለት ልጅ እያሱ ላይ የሆነው ነው። ልጅ እያሱ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ ሕጋዊ ማዕቀፍ የነበረው ቢሆንም አቅም የነበራቸው አካላት ግን ከጎኑ አልነበሩም። ከልጅ እያሱ ይልቅ ለተፈሪ መኮንን ቅርበት የነበራቸው አካላት የልጅ እያሱን በአጤ ምኒልክ የተሰጠ ንግስና (በወቅቱ ሕጋዊ፣ ወይንም ምክንያታዊ) በሀይላቸው ወደ ተፈሪ አሸጋግረዋል። ልጅ እያሱ ሕጋዊ ወይንም ምክንያታዊ የነበረ ቢሆንም ልጅ እያሱ ግን ሴራውን በመረዳት ለዚህ ስልጣን ብቁ፣ ለውጡንም የሚሸከም ሆኖ እንዳልተገኘ ድርሳናት ይገልፃሉ። በስልጣኑ መሰረት ፖለቲካውን ከመሸከም ይልቅ የልጅነት ፍላጎት ያመዘነበት ተግባር ሲፈፅም እንደነበር ይነገራል።
~ ልጅ እያሱ ወደስልጣን ከመምጣቱ በፊት ሕዝብ የተመረረባቸውን ጉዳዮች በመፍታት ትልቅ ድርሻ በመወጣት፣ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ችግር ያልነበር ቢሆንም አቅም የነበራቸውና ቤተ መንግስት አካባቢም ሆነ በቅርብ ርቀት የነበሩትን ሰዎች ሴራ የመበጣጠስ ወይንም በማቅረብ ግን ይህ ነው የሚባል ስራ አልሰራም። አብዛኛዎቹን ይንቃቸዋል። ሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮችን በልጅነት፣ በየዋህነት ሲያልፍ አቅም የነበራቸው አካላት የሞት ሽረታቸውን ከስልጣኑ አውርደው ከተፈሪ መኮንን ጋር ቆመዋል።
~የዶክተር አብይ መንግስት የልጅ እያሱ አይነት እጣ እንዳይገጥመው ያሰጋል። ልጅ እያሱ ከንጉሳዊ ስርዓቱ የወጣና ሕጋዊ ንግስና ያገኘ ነበር። በዛ ዘመን ሕዝብ የተለየ መሰረተ ልማት አይፈልግም ነበር። የሚፈልገው ሰላምና ዘመኑ ድርቅ አለመሆኑን ብቻ ነበር። “በእያሱ እህል ነው ትራሱ” ይባል ነበር ይባላል ያ ዘመን። በዛ ወቅት የነበረው ዘመን አንድን የንግስና ስርዓት ሰላምና ጥጋብ ከመሆን ብዙ ነገር አይጠብቅም። ልጅ እያሱ የሌባሻይና ሌሎች ስርዓቶችንም አስወግዷል። ከእኛ ዘመኑ አዋጆች በላይ ለውጦቹ ለዛን ወቅት ሕዝብ ሊያደስቱ ይችላሉ። በእነ እያሱ ዘመን በሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ትክክለኛውን የንግስና ተዋረድ መውሰድ በቂ ነበር፣ ለሕዝብ የምኒልክ ኑዛዜ በቂ ነበር!
~ዶክተር አብይ አህመድ ከስርዓቱ የወጣ ነው። ከእያሱ የሚለየው ዶክተር አብይ የወጣበትን ስርዓት በግልፅ የሚቃወመው ሕዝብ በርካታ መሆኑ ነው። የዶክተር አብይ ዘመን ከእያሱ የሚለየው ከቀደመው ስርዓት ቅቡልነት ሳይሆን፣ ከቀደመው ስርዓት ክፉነት የተለየ ነው ተብሎ በመታሰቡ ነው። ይህኛው የዶክተር አብይን እጣ ከልጅ እያሱ የባሰ ያደርገዋል።
~ ዶክተር አብይ አህመድ እንደ ልጅ እያሱ በህዝብ ዘንድ ተቀባትነት ቢኖረውም በአንጋሾች ዘንድ ግን መርህ የጣሰ ተደርጎ ተወስዷል። ልጅ እያሱ የዘውዳዊ ስርዓቱን ስርዓቱ መርሆች አፈነገጠ ተብሎ በአንጋሾች ሲወቀስ እንደነበረው ዶክተር አብይም ከኢህአዴግ መርህ ወጥቷል ተብሎ እየታኘከ ነው። በዘመኑ አንጋሾች። ልጅ እያሱ “ስራውን ጥሎ እየዞረ ነው” ተብሎ ሲወቀስ እንደነበረው፣ ዶክተር አብይም ብክነቱ በዝቷል። ልጅ እያሱ አንጋሾቹን ንቆ፣ ሴራቸው ላይ ሳያተኩር የራሱን ተግባር ይከውን እንደነበረው፣ ዶክተር አብይም “መደመር” በሚለው መርህ የቀን ጅብ ያላቸው ላይ ቸልታን መርጧል። ልጅ እያሱ የአንጋሾችን ሀይል እያወቀ በንጉስ ሚካኤልና የምኒልክን ኑዛዜ ሰምቷል ባለው ሕዝብ ተስፋ እንዳደረገው ሁሉ፣ ዶክተር አብይም “በቲም ለማ” እና “መደመር” ሲዘምርለት ባጨበጨበው ሕዝብ ተስፋ አድርጓል።
~ቅቡልነትም፣ ለውጥም ሳያንሰው አንጋሾችን ንቆ የራሱን ተግባር ብቻ የከወነው ልጅ እያሱ ለጉብኝት ከሄደበት ሳይመለስ ስልጣኑን አንጋሾቹ የወደዱት ተፈሪ ወሰደው። የዘመኑ አንጋሾች የትህነግ ጀኔራሎች ናቸው፣ የትህነግ የካድሬና ደሕንነት መዋቅር ነው። እነዚህ በትህነግ/ህወሓት ሰፈር ብቻ ሳይሆን በብአዴን፣ በኦህዴን፣ በዴህዴን…በሌሎቹም ሰፈር አሉ። ምን አልባት ዶክተር አብይን ከእያሱ የሚለው ሕዝብና ተቃዋሚ ከድሮው የተሻለ ሀይል ያለው መሆኑ ነው። ግን አንጋሾቹም ከሕዝብ በላይ ኃይል አላቸው። ማፈኛው ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በእስር የሚያናክሱበትን ዘመናዊ ሴራ ተክነውበታል። እንዲያውም በእያሱ ዘመን ከነበሩት አንጋሾች በላይ የተደራጁና የከፉ መሆናቸው ነው። አንጋሾቹ ልጅ እያሱን “ልጅ ነው” ብለው ይንቁት እንደነበረው ሁሉ የዘመኑ አንጋሾች የዶክተር አብይህን “መደመር፣ ፍቅር፣ ይቅርታ” ማጥቂያ አድርገውታል።
~የዶክተር አብይ ዘመን አንጋሾች ጥርሳቸውን የነከሱት በሴራ እንደመሆኑ ይህን የዶክተር አብይ ፖለቲካ ንቀውታል። ዶክተር አብይ አህመድ ንጉሱን ለማምለክ ምንም ያልቀራቸውና በ1953 ዓም ሙከራ ካደረጉት፣ የመንግስቱን መርህ መርሃቸው ያደረጉትና በ1981 በ”ጓድ መንግስቱ” ላይ ከተነሱት፣ እንዲሁም ትህነግ ስር ሰልጥነው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደረጉ ከተባሉት የተለየ በልጅ እያሱ ዘመን ከነበሩትም በባሰ የማይቀበሉት አንጋሾች ጋር ይገኛል። እንዲያውም የእያሱ ዘመን ሳይሻል አይቀርም። የእያሱ ዘመን አንጋሾች አጤ ምንሊክን የሚያስቡትን ያህል፣ የአብይ ዘመን አንጋሾች ትህነግ/ህወሓት ንጉሳቸው ነው። ለአብይ ዘመን አንጋሾች ዶክተር አብይ ትህነግ ከሚበል “ንጉስ” በተቃራኒ የቆመ እንጅ ሕጋዊ ስልጣን የያዘ አድርገውም አያስቡትም። ለማምለክ በሚቀርቡት መለስ ዜናዊና ከእሱ በላይ ድርጅት የለም ከሚሉት ትህነግ መርህ ስልጣን የያዘ “ህገ ወጥ”፣ ትህነግና መለስ ዜናዊ አሰፈኑት ያሉትን ህግ የጣሰ አድርገው ይወስዱታል። እነሱ ይህን ያህል ርቀት እያሰቡ ግን ዶክተር አብይ እንደ ልጅ እያሱ እየዞረ “መደመር”ን ይሰብካል። ለራሱም ሆነ ወሳኝ ለተባሉ አካላት ጥበቃ አያደርግም። በአንጋሾቹ የተጠሉ፣ ተጠልተው የተባረሩ መኮንኖችንና ሌሎችንም አንጋሾችን ለመቀነስ እየተጠቀመ አይደለም።
~ ይህን ሁሉ ስናይ ዶክተር አብይ አህመድ በሚያምኑት ሳይሆን፣ ከቆዩበት ስርዓት ያፈነገጠ በሚመስላቸው፣ በግልፅም አፈንግጧል እያሉ በሚወነጅሉት አንጋሾች ስልጣኑን የሚያጣበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ለመገመት ያስችለናል። ልጅ እያሱ የሕዝብ ተቀባይነት ሳያጣ፣ የለውጥ ጅማሮው ሳያንሰው እየዞረ፣ በአንጋሾቹ ስልጣኑን እንዳጣው ዶክተር አብይም ይህ እጣ እንዳይገጥመው ያሰጋል። ስጋቱ ከልጅ እያሱም የባሰ ይመስላል። ይህ ስጋት ግን ለአብይ ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያም ጭምር እንጅ! አንጋሾቹ ያኔ ተፈሪን ያነገሱትን ያህል ዛሬ ተፈሪን የመሰለ ሰው የላቸውም። አጋጣሚውን ከተጠቀሙት፣ አብይም አጋጣሚውን ከተነጠቀ አንጋሾቹ የሚያመጡት ስለ ሀገርና ሕዝብ ከማሰብ ይልቅ እጅግ ለጠበበ ጥቅም የሚያስቡት የቀን ጅብን መሆኑ ስጋቱን የከፋ ያደርገዋል!