ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ (ይገረም አለሙ)

ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ (ይገረም አለሙ)

ዛሬ ጥቅምት አንድ ቀን 2009 ዓ.ም. ቀትር ላይ በሞት የተለዩንን ኢ/ር ኃይሉ ሻውልን ወደ ዘለዓለማዊው ቤት ለመሸኘት አዲስ አበባ አራት ኪሎ ከሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተናል። እዛው የተገናኘን ሰዎች ዝናቡ መቆሚያ ቢያሳጥንም አንድ ጥግ ይዘን አስክሬናቸው እስኪደርስ ወግ ይዘናል። ኢ/ር ኃይሉን ለመጀመሪያ ግዜ ያወቅናቸው በመአህድ ከዚያም በመኢአድ ቀጥሎም በቅንጅት፤ እንደገና ተመልሶ በመኢአድ በመሆኑ ከዚህ እውቀታችን በመነሳት ከፊት ወደ ኋላ እያስታወስን ስናነሳ ስንጥል የመአህድ መስራችና ፕሬዝዳንት የነበሩትንና በእስር ተሰቃይተው በግፍ የሞቱትን ፕ/ር አስራት ወልደየስን አስታወስን። የገደሉንንም የሞቱልንንም እኩል የምንረሳ ምን ጉዶችን በማለትም ራሳችንን ወቀስን።

ለኢ/ር ኃይሉ አስክሬን ማረፊያ የተዘጋጀው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ርጥቡ ሬሳ ደረቅ ያስነሳ እንዲሉ ሆኖ፤ 18 ዓመት ወደ ኋላ አስጉዞ የአስራት አስክሬን በዚህ ቦታ እንዳያርፍ መደረጉን አስታወሰን። ክፋቱ ገደብ፣ የበቀል ስሜቱ ርካታ የለሽ የሆነው ወያኔ ገድሎ ባለመርካት የቀብር ቦታ መከልከሉ አረመኔነቱን የሚያሳይ ቢሆንም፤ ምን ያህሎቻችን ነን ይህን እምናስታውስ ብለን ራሳችንን ጠየቅን። ከቀብር ፍጻሜ በኋላም ወረድ ብለን ባለወልድ የሚገኘውን የአሥራት የቀብር ቦታ አየን። ኃይሉን ልንቀብር ሄደን አስራትን አስታውሰን ይበልጥ አዝነን ራሳችንን ወቅሰንና የመኢአድ ሰዎችን ታዝበን ተመለስን። ለምን ብትሉ እነርሱም እንደማንኛውም ሰው አስራትን በመርሳታቸው።

የወያኔው አብዮት በፈጠረው የፖለቲካ ስካር፤ ሀገሬ ወገኔ ብሎ በኢትዮጵያ ሁሉ ተበትኖ በሚኖረው አማራ ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የተፈጸመበት ጥቃት ነበር እውቁን ቀዳጅ ሐኪም በሕክምና የተያያዙትን ነፍስ አዳኝነት ወደ በፖለቲካ ትግል ሕይወት ታዳጊነት ለመለወጥ አስገድዶ፤ የመአህድ ፕሬዝዳንት ለመሆን ያበቃቸው። መአህድም በአጭር ግዜ ገነነ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን በመወከል በሰኔው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው፤ ይህ ጉባዔ በኤርትራ ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን የለውም ብለው የተቃወሙና፤ ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ብቸኛ ሰው በመሆናቸው፤ በወያኔ ተጋዳላዮች ዓይን የገቡት አሥራት በሳቸው ፕሬዝዳንትነት የመአህድ ባልተጠበቀ ፍጥነት ጎልቶ መውጣት ጥርስ አስነከሰባቸው።

ትናንትን እየረሱ በዕለት ተዕለቱ በመጮህ በሽታ የተለከፍን በመሆናችን እንጂ ወያኔ ማንነቱንም ምንነቱንም በፕ/ር አስራት ላይ በፈጸመው ሕገ ወጥና ኢሰብዓዊ ድርጊት አሳይቶን ነበር። ከዛ በኋላ በፖለቲከኞችም ሆነ በጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመው ሁሉም በአስራት ላይ የደረሰ ነው።

በደብረ ብርሃን በተጠራ ስብሰባ ላይ ካደረጉት ንግግር አንድ ዐረፍተ ነገር ተመዞ ህዝብን ለአመጽ የማነሳሳት ንግግር አደረጉ ተብሎ ተከሰሱ፤ ይሄ ጉድ ሲባል ከጎጃም ከመጡ ገበሬዎች ጋር በጽ/ቤታቸው አመጽ ስለማስነሳት መክረዋል የሚል ክስ ተጨመረ። በየፖሊስ ጣቢያው እየተጠሩ በዋስ ሲመለሱ ቆይተው 86 መጨረሻ ግድም ዳግም ላይመለሱ ወህኒ ወረዱ። የሐሰት ምስክር አሠልጥኖና አስፈራርቶ ማስመስከር፣ በትዕዛዝ የሚፈርዱ ዳኞችን መድቦ ማስፈረድ፣ ጠያቂን ማንገላታት ሲላቸውም መከልከል የመሳሰሉት እስከ ዛሬም የሚጮኽባቸው ሕገ ወጥና ኢሰብዓዊ ድርቶች ሁሉ በአስራት ላይ ተፈጽመዋል። ይህም ብቻ አይደለም የስንቱን ሕይወት የታደጉ ሰው ሕክምና ተከልክለው በሽታቸው ከተባባሰ በኋላ፤ ለይስሙላ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲተኙ ተደርጎ መጨረሻም የማይድኑበት ደረጃ መድረሳቸው ሲረጋገጥ እጃችን ላይ ከሚሞቱ ተብሎ አሜሪካን ሀገር ተልከው ብዙም ሳይቆዩ ነበር አስክሬናቸው የተመለሰው።

በወቅቱ ርሳቸውም በከፍተኛ የጤና መታወክ ላይ የነበሩትና ብዙም ሳይቆዩ የተከተሉዋቸው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን አሜሪካን ሀገር በተካሄደው የአስክሬን ሽኝት ላይ በድጋፍ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በሽታህ ምን እንደሆነ እንኳን ሳይታወቅ ተለየኸን በማለት እንደገለጹት፤ አስራት በእስር ቤት ተሰቃይተው ሕክምና ተነፍገው መሞታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለሞት ያበቃቸው በሽታ ምንነት እንኳን አለመታወቁ የሚቆጭ የሚያንገበግብ ነበር። ቁጭት መንገብገባችን ከአንድ ሣምንት አላለፈም እንጂ።

ድርጅታቸው መአህድ በሐሰት ክስ የታሰሩት መሪያችን ይፈቱ ማለት ቀርቶ ሕክምና ያግኙ ብሎ የሰላማዊ ሰለፍ ጥሪ አለማድረጉ፤ ከሞቱም በኋላ በሽታቸው አልታወቀም እየተባለ የአስክሬን ምርመራ እንዲደረግ አለመጠየቁ፤ ይህ ሁሉ ቀርቶ ወያኔ ሊያዝበት በማይገባው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስክሬናቸው እንዳያርፍ ሲከለክል ለምን ብሎ አለመከራከሩ ባሰቡት ቁጥር ልብ የሚያደማ ነው።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ግን ቀብራቸውን በደማቸው ጭምር አደመቁት፣ በሆታና በመፈክር ሸኑዋቸው ሁለት ወጣቶችም ተከተሉዋቸው። ለሚገጥመው ተቃውሞ ሁሉ ምላሹ ጥይት በሆነው ወያኔ ከቀብር መልስ ፓርላማው ጀርባ በር ላይ ነበር ሁለት ወጣቶች በጥይት የተመቱትና አንዱ ወዲያው ሲሞት ሁለተኛው ሆስፒታል ደርሶ ያረፈው። የወቅቱ የመኢአድ መሪዎች ግን ይህን የወያኔን ድርጊት ለማውገዝና የወጣቶቹን መስዋዕትነት ለማድነቅ ወይ ድፍረቱ ወይንም ፍላጎቱ አልነበራቸውም።

ወያኔ በበቀል የአስክሬን ማረፊያ ቢከለክላቸው፣ ድርጅታቸው በእስር ለመሰቃየታቸውም ሆነ በግፍ ለመገደላቸው ትኩረት ባይሰጠው፤ እኛም እስከ እስር ቤት አጨብጭበን እስከ ቀብር አልቅሰን ሸኝተን ብንረሳቸውም፤ ለሀገራቸውና ለወገናቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ልናሳንሰውም ሆነ ልናኮስሰው አንችልም። እኛ ለመስዋዕትነታቸው ክብር ሰጥተን ባናስታውሳቸው፤ ለውለታቸው ባለ አደራ ሆነን ባንገኝ፤ ነገ ታሪካቸውን እያወሳ የሚዘክራቸው አርኣያነታቸውን እያደነቀ የሚከተላቸው ትውልድ ሊመጣ ይችላል። መጥኔ ለእኛ እንጂ የሚገድሉንንም የሚሞቱልንም እኩል ለምንረሳው።

የኢ/ር ኃይሉንም የፕ/ር አስራትንም ነብስ ይማር!

LEAVE A REPLY