ሃገራችን “ምርጫ አሁኑኑ” የሚባልባት ነች? | በመስከረም አበራ

ሃገራችን “ምርጫ አሁኑኑ” የሚባልባት ነች? | በመስከረም አበራ

ሃገራችን ለፖለቲካ ህመመሟ ፈውስ በምታገኝበት ወይም ጨርሳ የአልጋ ቁራኛ በምትሆንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ዋነኛ ህመሟ የዘር ፖለቲካ አመጣሽ ደዌ ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ በደም ሥሯ ገብቶ መላ አካሏን የሚያናውጣት ይህች ደሃ ሃገር ሲባል የሰማችው እንዳይቀርባት ስታደርግ የኖረችው ሃገራዊ ምርጫም ቀነቀጠሮው ደርሷል፡፡ እንደ ፅዋ ማኅበር ወራቱን ጠብቆ ምርጫ ማድረግ እና ተመልሶ በዘር ፖለቲካ ኋላ ቀር ዘይቤ መመላለስ ከዲሞክራሲዊ ምርጫ ትርጉም ጋር የማይዛመድ ልማዳችን ነው፡፡ ይህ ልማዳችን የፖለቲካችንን ጉልበት ለዝለት ዳርጎ እንዳንራመድ ሲያንፏቅቀን የኖረ ክፉ ቁራኛችን ሆኖ አለ፡፡

ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ነው ቢባልም ሁሉም ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ሊሆን አይችልም፡፡ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር የሚዛመደው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ እንደ ሰንበቴ ወር እየጠቁ ምርጫ ማድረግ ለሃገር ዲሞክራሲን አያመጣም፡፡  በአፍሪካ አህጉር የሚደረጉ እንደ ትጥቅ ትግልም የሚሞክራቸው ምርጫዎች ለአምባገነኖች የተመርጫለሁ ሽንገላ ይረዱ ይሆናል እንጅ ለሃገር እና ለህዝብ ዲሞክራሲን ሊያመጡ አይችሉም፡፡

ሃገራችንን ጨምሮ ከምርጫ ማግስት ደም መፋሰስን እና በፍርድ ቤት መካሰስን አስከትሎ የሚመጣው የአፍሪካ ሃገራት ምርጫ ለህዝብ ጭንቅን እንጅ ደስታን ይዞ አይመጣም፡፡በቅርቡ በኬንያ የተደረገው(የምርጫ ኮሚሽነሩን መሰዋት ያደረገው) ምርጫ ሲቃረብ የሃገሪቱ ህዝብ ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ በየእምነት ተቋሙ ሱባኤ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ጎረቤት ሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣ዩጋንዳ በተመራጭ አምባገነኖች የሚንገላቱ፣ የእኛ ቢጤ “የምርጫ ሰለቦች” ናቸው፡፡

በሃገራችን የተደረጉ ምርጫዎች ታሪካዊ ዳራ ቢጠና የህወሃትን በተለይ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊን ጉልበት ከቀን ቀን እያበረቱ በስተመጨረሻው ወደ ተሟላ ተመራጭ አምባገነንነት ያደረሱ ሃዲዶች ናቸው፡፡በኢህአዴግ ስር የተደረጉ ምርጫዎች የእድገት ጫፍ በፓርላማው መቀመጫ ሁሉ የአንድ ፓርቲን ካድሬዎችን መኮልኮል ነው፡፡ተገዳዳሪ ለማይወደው ኢህአዴግ ይህ ብቻ ድል ሆኖ አሳርፎ አያስቀምጥም፡፡ይልቅስ የድሉ ማህተም ከፓርላማ ወንበር ርቀው በቆሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጓዳ ገብቶ ህብረታቸውን ማፈራረስ፣ስማቸውን ከህይወት መዝገብ መሰረዝ ነው፡፡

ይህን ካደረጉ በኋላ ደግሞ ተቃዋሚ ጠፋ እንዳይባል ነፍስ ያላቸውን ተቃዋሚዎች ለማፍረስ የተጠቀመባቸውን የፖለቲካ ወንጀለኞች ተቃዋሚ ብሎ ደሞዝ ሳይቀር እየከፈለ የፈለገውን ያናግራቸው ነበር፡፡የሚወደውን ወንበሩን ለመጠበቅ የራሱን ተቃዋሚ ፈጥሮ ደሞዝ መክፈል ድረስ ርቆ ወደታች የሚምዘገዘገው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ጠላት ከሩቅ ሲጠብቅ አቤት ወዴት ሲያስብላቸው የኖሩ የራሱ ሎሌዎች ባላሰበው መንገድ ገፍተር አድረጉት፡፡ የገዛ አቤት ባዮቹ በፅኑ ፍቅር የጣለውን ወንበሩን ሲይዙ ራሱን አግዝፎ የሚያየው ህወሃት ዕብድ የሚያደርገውን ንዴቱን ብቻ ይዞ ቀረ፡፡

ህወሃት ቀርቶ እኛም ባላመንነው መንገድ የፖለቲካችን/የኢኮኖሚያችን መዥገር የሆነው የህወሃት አገዛዝ ቢወገድም ዲሞክራሲን አርቆ ለመቅበር ሳይታክት ሲሰራው የኖረው ስራው ግን ለሃገራችን ዲሞክራሲ ትልቅ ፈተና ደቅኗል፡፡ህወሃት ዘረፋውን ለሚጋርድለት  ስልጣኑ ሲል ያጠፋው ጥፋት የትየለሌ ቢሆንም በሃገራችን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ባህል ስር እንዳይይዝ ያደረገው ድርጊት ይቅር ለማለት አስቸጋሪው ጥፋቱ ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በመሰረታዊነት የሃሳብ ውድድር ነው፡፡የሃሳብ ውድድሩ መሰረት የሚያደርገው ተወዳዳሪዎቹ የሚያመጡት የፖሊሲ ሃሳብ እንጅ የሚናጉትን ቋንቋ አይደለም፡፡ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ሃሳብ የሰማው ህዝብ በምርጫ ካርዱ ለሚቀጥሉት አራት ወይም አምስት ዓመት ማን ፖሊሲ ያውጣልኝ የሚለውን ይወስናል፡፡ ህዝብ የተገዳዳሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ ለመስማት፣ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የፖሊሲ ብልጫቸውን ለህዝብ ለማቅረብ ህዝብ እና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ያለገደብ መገናኘት አለባቸ፡፡የውድድሩ ሜዳ ለማንም ያላዳላ ፍትሃዊ መሆን አለበት፡፡እድሜው ለመምረጥ መመረጥ የደረሰ ሰው ሁሉ መምረጥም መመረጥም መቻል አለበት፡፡ህዝቡም ሆነ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በምርጫው አስፈፃሚዎች ላይ እምነት መጣል አለበት፡፡ይህ በስተመጨረሻም በሃገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የምርጫ ውጤቱን አምኖ ለመቀበል ያስችላል፡፡

ወቅታዊ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንቅፋቶች

አሁን ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ከላይ የተቀመጠውን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሰረታዊ ይዘት ባሟላ ሁኔታ ማድረግ የሚያስችል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይደረግ አይደረግ ከመባሉ ቀደም ብሎ መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በግሌ ምርጫውን በታቀደለት ጊዜ ማድረግ የማይቻል ብቻ ሳይሆን አደገኛ መስሎም ይሰማኛል፡፡ምርጫውን በቀጠሮው ለማድረግ የማያስችሉትን ምክንያቶች በሶስት መክፈል ይቻላል፡፡

  1. ህወሃት/ኢህአዴግ ሰራሽ እንቅፋቶች

የመጀመሪያው እና መሰረታዊው ችግር ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ህወሃት ለስልጣኑ እና ዘረፋው ሲል ተገዳዳሪን ድምጥማጥ ለማጥፋት ያደረገው (ደደቢት ላይ ካደረገው ያላነሰ) ተጋድሎ ነው፡፡ በዚህ እጅግ አሳዛኝ ስራው አንድነትን የመሰለ ጠንካራ ፓርቲ አጥፍቷል፡፡ በትንግርት የተረፈው ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን መሪዎቹን ለእስርቤት ገብሮ በመኖር እና ባለመኖር መሃል ብቅ ጥልቅ ሲል የኖረ ነው፡፡ መኢአድም ገና ከጠዋቱ ያለ ርህራሄ በህወሃት ሰደፍ ሲደቆስ፣ ሰላማዊ ተቃዋሚ ሆኖ ሳለ እንደ ታጣዊ ቡድን በእጅጉ ሲታደን የኖረ፣ እስከዛሬ መኖሩም የሚገርመኝ ፓርቲ ነው፡፡ ኢዴፓም ቢሆን በተመሳሳይ እንግልት የኖረ ከመሆኑም ባሻገር በቅርቡ ቤቱን ከማጥራቱ በፊት ከአንዳንድ መሪዎቹ ሁኔታ አንፃር ከህወሃት ጋር ያለው ግንኑነት በህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነበር፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲህ ባለ የህወሃት/ኢህአዴግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሰፈር ጉልበተኛ አይነት ስራ በከፍተኛ መገለል እና የመጥፋት አደጋ ውስጥ በኖሩበት ዘመን አሁን እንደ ፓርቲ ይወዳደር የሚባለው ኢህአዴግ ደግሞ በፖለቲካው መስክ ሃገር ምድሩን በግድም በውድም አባል አድርጎ ኖሯል፡፡በኢኮኖሚው መስክ ፓርቲ መሆኑ ሳያግደው ሲነግድ ኖሯል፡፡ብቻውን ተቆጣጥሮ ልማታዊነቱን ሲነዛበት የኖረው የህዝብ ሚዲያ አሁንም በእጁ ነው፡፡በንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ሊያነቁበት፣ ከህዝብ ጋር ሊገናኙበት የሚችሉት የግሉ ሚዲያ በህወሃት/ኢህአዴግ ሰደፍ ተገዶ ተዘግቶ ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በአመዛኙ ህዝብ ታግሎ ያመጣው ለውጥ ወሮታ በተለምዶ የለማ/ገዱ ቡድን ለሚባለው ለኢህአዴግ ፓርቲ አፈንጋጮች እየተሰጠ ነው፡፡ይህ የቅድመ ለውጥ ምክንያት በድህረ ለውጥ ከተባባሰው የዘር ፖለቲካው ጋር ሲደመር ወደ ሁለተኛው የምርጫ እንቅፋት ያደርሰናል ፡፡

  1. ከለውጡ ጋር የሚዛመዱ እንቅፋቶች

ህወሃት/ኢህአዴግ ተደላድሎ ተቀምጦ ሃገርን አሳር መከራ ሲያሳይ የኖረበትን አገዛዝ ያስወገደው ህዝባዊ ትግል ተስፋንም ስጋትንም ያዘለ ድባብ አለው፡፡ተስፋው አዲሱ የለውጥ አመራር ሃገሪቱን ሊያጠፋት ደርሶ የነበረውን መከፋፈል በማጠየቅ የጋራ ሃገርን ለመገንባት የሚያደርገው ጉዞ ሊያደርሰን የሚችለው ሃገራዊ ብልጽግና ሲሆን ስጋቱ ደግሞ ይህን ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችለው የዘር ፖለቲካ ወለድ መተላለቅ ነው፡፡ ለውጡ ብዙ ጥሩ ብስራቶች ቢኖሩትም እጅግ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ መርገሞችንም ያመጣ፣ ወደፊትም የባሰውን ሊያመጣ የሚያስችል አዝማሚያ ያለው ነው፡፡

ይህ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ ተዘርቶ የበቀለው እና እንዲህ ለውድመት ብቁ የሆነው ለውጡ በቆየበት የስምንት ወር እድሜ አይደለም፡፡ ዘረኝነት በእንክብካቤ አድጎ ያሸተው ህወሃት/ኢህአዴግ በኖረበት ረዥም ዘመን ነው፡፡ህወሃት አስሮ ያሳደገው ዘረኝነት የሚባል አውሬ ጎልምሶ፣ ከጎሬው ወጥቶ አሳዳጊውን ቦጫጭቆ መግደሉ ደግ ቢሆንም ህወሃትን አጠፋሁ ብሎ ዝም ብሎ የማይተኛ መሆኑ ነው ጭንቁ፡፡ህወሃትም ቢሆን ራሱ ተንከባክቦ ያሳደገው ዘረኝነት ራሱንም እንዳጠፋው ቢያውቅም ከእርሱ መጥፋት በኋላ ሃገሪቱ በዘረኝነት ጦስ ስትታመስ እሱ ስለሌለ የመጣ ችግር እንጅ እሱ ያልፈጠረው ችግር አድርጎ ለማውራት አይሰንፍም፡፡ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ በስልጣኑ ወራት ዘቅዝቆ ሲገርፋቸው ከነበሩ አክራሪ የዘር ድርጅቶች ጋር እየተገናኘ የሃገርን ጣር ለማብዛት እንደሚሰራ የታወቀ ነው፡፡

ህወሃት እና የቀድሞ ጠላቶቹ የአሁን ወዳጆቹ አክራሪ የዘር ፖለቲከኞች ገንዘብ ጠመንጃቸውን አዋህደው በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን እያስጨነቁ፣ሃገር ወደ ገሃነም በር የምትደርስበትን መንገድ እየተለሙ ይገኛሉ፡፡ከዚህ ስራቸው አንዱ የሃገሪቱ ምርጫ በተያዘለት ፕሮግራም ይደረግ የሚለው ህጋዊ መሰል ጥያቄያቸው ነው፡፡ይህን ጥያቄ በዋናነት የሚያቀነቅኑት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ሲሆኑ ህወሃትም እንደሚፈልገው ጥናት አቀርባለሁ ብለው መቀሌ የነጎዱት አቶ በረከት ጠቆም አድርገዋል፡፡ ምርጫው በሰዓቱ ይደረግ የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ መሪዎች አክራሪዎቹ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቅስ መሃል መንገድን እንደሚሹ አጥብቀው ሲናገሩ የኖሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሳይቀሩ “ምርጫው ነገ ቢደረግ እኛ ደስታችነ ነው” ሲሉ ስሙን በማላስታውሰው ቴሌቭዥን ቀርበው ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡

የዘር ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ምርጫው በሰዓቱ እንዲደረግ የሚፈልጉበት ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከድሮ እስከ ዘንድሮ ሲመረጡ የኖሩት እትብታቸው በተቀበረበት መንደር እየሄዱ ነው፡፡ዕትብታቸው በተቀበረበት መንደር እስከሄዱ ድረስ  እንደሚመረጡ እርግጠኛ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል  ይህን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር መረራ በአንድ ወቅት ከኢሳቱ አቶ ግዛው ለገሰ እና ሟቹ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ጋር ባደረጉት ቆይታ “ግፈቃደ አንተም አምቦ የተወለድክ(ያደግክ?) ቢሆንም አሁን አንተ እና እኔ ለምርጫ ልንወዳደር አምቦ ብንሄድ የምመረጠው እኔ እንደሆንኩ ጥርጥር የለኝም” ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የምንረዳው በሰፈሩ የምርጫ ጣቢያ ብቻ ለመመረጥ የተሰየመ የዘር ፖለቲከኛ በምርጫ ለማሸነፍ የሚሰራው አንዳች ነገር የለም፡፡ አሸናፊነቱን የሚያፀናው ስራ ተሰርቶ ያለቀው በተፈጥሮ አደራጅነት፣ ከዛች መንደር፣ የዛን አካባቢ ቋንቋ ከምትናገር እናት የተወለደ ቀን ነው፡፡ እንዲህ ባለው በተፈጥሮ አጋፋሪነት በሚያልቅ መምረጥ መመረጥ ውስጥ የሃሳብ ውድድርን ገበያ አንደኛ የሚያደርገው የዘመናዊ ዲሞክራሲ ምርጫ እጣ ፋንታ የለውም፡፡ ምርጫ ይኖራል ዲሞክራሲያዊ ግን አይደለም፡፡ ምርጫው የሚኖረውም እዛው ሰፈር እትብቱ የተቀበረ ሌላ ተገዳዳሪ ከመጣ ነው እንደጂ የሌላ ሰፈር ሰው ድርሽ እንዳይል የእትብት መማዘዙ ፖለቲካ ያግዳል፡፡ እንዲህ ባለው ውድድር ለማሸነፍ ደግሞ ክርክሩ የእናት የአባት የዘር ንጥረት ይሆን ይሆናል እንጅ የሃሳብ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ውስጥ ዲሞክራሲን መፈለግ ላምም ሳርም በሌለበት ኩበት መልቀም ነው!

በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ ተፈጥሮን ሳይሆን ተመክሮን እና ሃሳብን መሰረት ስለሚያደርግ ትልልቅ ስራዎች የጠብቁታልና ምርጫ ነገ ይሁን ለማለት አይደፍርም፡፡ አንደኛው ትልቅ ፈተና የዘር ፖለቲካ አለቅጥ እጅ እግሩን ዘርግቶ ተንሰራፍቶ በኖረበት ሃገር የፖሊሲ ሃሳብን ይዞ የወንዙ ልጆች ባልሆኑ ሰዎች ፊት መቅረቡ ነው፡፡ የሰፈሩን ሰው ብቻ እንዲያምን ሲነገረው የኖረ ህዝብ የሌላ ሃሳብ መስማት ቀርቶ በሰፈሩ መርገጡ ራሱ ሊያስቆጣው እንደሚችል አዝማሚያዎች እያየን ነው፡፡እድል ቀንቶት፣ሃሳብ የሚሰሙ ዜጎች አግኝቶ፣በፖሊሲው መስህብ ማርኮ የመመረጥ እድል ቢያገኝ እንኳን የምርጫውን ውጤት የሚቀበለው ሰው ምን ያህሉ ነው የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

  1. ህገ-መንግስት ወለድ እንቅፋቶች

በሃሳብ የበላይነት ላይ የሚቆመው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተፈጥሮን አጋፋሪነት ብቻ ተማምኖ ከሚቀመጠው የዘር ፖለቲካ ምርጫ ጋር ዝምድና የለውም፡፡ አሁን ሃገራችን የምትመራበት ህገ-መንግስት ደግሞ የዘር ፖለቲካን በህግ ያነበረ፤ የአዋቂዎች አካታች የመምረጥ መመረጥ (Adult Universal Suffrage) መብትን በተዘዋዋሪ የሚነፍግ ነው ፡፡ ይህ ህገ-መንግስት ዘር ቆጥሮ በከለለው ክልል ሰባት ጉልበቱ ያልተወለደ ሰው መራጭ ይሆናል እንጅ የመመረጥ መብት የለውም፡፡ ጭራሽ እሱ መጤ/ሰፋሪ/ወራሪ እየተባለ በሚኖርበት መሬት በወቅቱ የማይኖሩ ግን ከሃምሳ ስልሳ አመት በፊት እዛ ሃገር እንደ ተወለዱ የሚታመንባቸው፣ ሰባት ጉልበታቸው ተቆጥሮ ሃገሬነታቸው የተረጋገጠ ሰዎች ተመራጭ ሆነው ይመጣሉ፡፡በዚህ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርት የሆነው በአካባቢው ከሁለት አመት በላይ መኖር እና እድሜ ለመመረጥ መድረስ ዋጋ የላቸውም፡፡

እንዲህ ያለው ህገ-መንግስት አንድ ዓረፍተ-ነገሩ ሳይነካ፣የምርጫው ቀን አንድ ሰኮንድ ሳያልፍ ምርጫው ይደረግ የሚሉ የዘር ፖለቲካ መሪዎች ፍላጎት የሃሳብ ዘመን ሳይመጣ ፣በግርግር ስልጣን ላይ መቀመጥ እና በጥፋቱ ብዛት እየተጠላ ያለውን፣የህልውናቸው መሰረት የሆነውን የዘር ፖለቲካ ከመጥፋት ታድጎ  ማስቀጠል ይመስላል፡፡ የዘር ፖለቲካ የሚመቸው ዘራቸውን ጠርተው ብቻ ያለ ልፋት ስልጣን ላይ ለሚቆናጠጡ ልሂቃን እና ቅዝምዝምን ዝቅ ብለው የሚያሳልፉበት ትርፍ ሃገር ላላቸው አክቲቪስቶች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግላዊ ጥቅማቸውን እና ዝናቸውን ለለማጣት ሲሉ ብቻ የዘር ፖለቲካ ወለዱ የዘር ፌደራሊዝም እጅግ ድንቅ እንደሆነ ቢሰብኩም በተግባር የሚታየው ተቃራኒው ነው፡፡

ከሁለት አመት በፊት በዘር ፖለቲካው ምክንያት የሚሞተው የሚፈናቀለው አማራው ብቻ ነበር፡፡ አማራው ደግሞ ለመጨቆን በሃገሪቱ ዳርቻ የተበተነ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ጠላት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበረ ዘርን መሰረት ያደረገው ፖለቲካ ችግር ፈጣሪ ተደርጎ ሳይታይ፣ጭራሽ አማራውን የቀጣ ጥሩ ለበቅ ተደርጎ ሲወሰድ ኖሯል፡፡

ሆኖም ዘመኑ ሲደርስ ኦሮሞው፣ ጌዲኦው፣ ሱማሌው፣ አማሮው፣ ጋሞው፣ ወላይታው፣ ጉራጌው፣ ከንባታው፣ ማረቆው፣ መስቃኑ፣ ቀቤናው ሁሉ የችግሩ ሰለባ ሲሆን የዘር ፖለቲካው አዋጭ እንዳልሆነ በተግባር እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የዘር ፖለቲካው ችግር ወስጥ እንዳለ የዘር ፖለቲካ መሪዎች አጢነዋል፡፡ በአኖሌ ሃውልት ዙሪያ ሲሰበሰብ ነበረው የአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ “ኢትዮጵያ ቅደሚ” ማለቱ በዘር ፖለቲካው ላይ ለመምሸቱ አይነተኛ ምልክትም፣ ከባድ ስጋትም ሆኖ ሳይቆጠር አልቀረም-በዘር ፖለቲከኞች ዘንድ፡፡

አብልቶ አልብሶ የሚያኖራቸውን የዘር ፖለቲካ ክፉ የማይወዱ የፖለቲካው ልሂቃን ታዲያ የህልውናቸውን ዋስትና ለመታደግ በመራወጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምርጫ ሳይውል ሳያድር ይደረግ የሚሉት መዋል ማደር ከመጣ የሃሳብ እና የምክንያታዊነት ፖለቲካ መድረኩን ሊረከብ ይችላል፤ይህ ደግሞ ተከታይ ያሳጣናል ከሚል ስጋት ነው ምርጫ አሁኑኑ እተባለ ያለው፡፡ በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ፓርቲዎች ህብረት እየፈጠሩ መሄዳቸው፣ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከማዘንበሉ ጋር ሲደመር የጎሳ ፖለቲከኞችን ጭንቅ ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡

”ምርጫው አሁኑኑ ይደረግ፣ የሽግግር መንግስት የሚል ድምፅ እንዳንሰማ” ባሉበት አፋቸው ድንገት ብድግ ብለው “እንደውም    ብሄራዊ የአንድነት እና የሽግግር መንግስት ይመስረትልን” እያሉ ያሉት ልብስ ጉርሳቸው የዘር ፖለቲካ ሊወድቅ ዘመም ዘመም ያለ ቢመስላቸው ነው፡፡

LEAVE A REPLY