ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በ7 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ የተሻሻለ ክስ...

ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በ7 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ የተሻሻለ ክስ አቀረበ

የኢፌድሪ አቃቤ ሕግ | የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ተኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት በ1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው፣ 2ተኛ ተከሳሽ ብርጋዴር ጀኔራል ጥጋቡ ፈትለ፣ 3ተኛ ተከሳሽ ሻለቃ ገብረስላሴ ገብረጊዮርጊስ፣ 4ተኛ ተከሳሽ ሻለቃ ፋሲል አበራ ሃይሉ፣ 5ተኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ 6ተኛ ተከሳሽ ወሰንየለህ ኃይለሚካኤል፣ 7ተኛ ተከሳሽ ህድአት ወልደተንሳይ እና 8ተኛ ተከሳሽ ዶ/ር መኮንን ገብረሚካኤል ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበውን የተሻሻለ ክስ ለመስማት ነው፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች በአሜሪካንም ሆነ በኢትዮጲያ ደረጃ የማይታወቅና ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የትምህርትና ስልጠና አፈፃፀም መመሪያ ውጭ “ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስትቲውት ኦፍ ቴክኖሎጅ” በሚል ሀሰተኛ ተቋም በማቋቋም ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የውል ስምምነት እንዲፈፀምና ክፍያው በውጭ ምንዛሬ እንዲሆን በማድረግ ና ድርጊቱ በኢትዮጲያ መንግስት እንዳይታወቅ መምህራን በቱሪስት ቪዛ ከውጭ በማስመጣት ና ያለ ትምህርት ዲግሪ በመስጠት እንዲሁም በማስተማር ሽፋን የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል መከሰሳቸውን ያሳያል፡፡

ሀሰተኛ የትምህርት ተቋሙ ማለትም “ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስትቲውት ኦፍ ቴክኖሎጅ” በታዳሽ ሀይልና በኦፕሬሽን ማኔጅመንት በማስተርስ እና በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት በ2006 የ1,393,300 ዶላር፣ በ2007 የ 698,650 እንዲሁም በ2008 ዓ.ም የ1,397,300 ዶላር ውል መፈረሙንና የትምህርት ካሬክለም ሳይቀረፅ ትምህርት መስጠት ተጀምሮ የነበረ መሆኑና በተመሳሳይ በ2009 ዓ.ም በኢንዱስትሪያል ኢኮኖሚክስ በማስተርስና በፒ.ኤች.ዲ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት የ1,903,225 የአሜሪካን ዶላር ከብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ውል መውሰዱን ከተሻሻለው የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ተከሳሾች በሶስት የተለያዩ የትምህርት መስኮች በአሜሪካንም ሆነ በኢትዮጲያ ደረጃ ከማይታወቅ የፈጠራ ተቋም ትምህርት ለመስጠት በሚል እሳቤ አራት ውሎችን በመዋዋል ለሀሰተኛ ተቋሙ 3,901,140.35 ዶላር ወይም 75,114,030.99 የኢትዮጲያ ብር አሜሪካን ሀገር በከፈታቸው የሂሳብ ቁጥሮች ገቢ ማድረጋቸውን የተሻሻለው የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ አብራርቷል፡፡
ስለሆነም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ተኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሾች ዐቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን የተሻሻለ ክስ መሰረት በማድረግ በፅሁፍ ያለቸውን አስተያየት ለ መጋቢት 9/2011 ዓ.ም እንዲያቀርቡ በይኗል፡፡

LEAVE A REPLY