የለማ መገርሳ ድምፅ በኦ ቢ ኤን ቲቪ እንዳይተላለፍ መከልከሉ በሠራተኞች ዘንድ ቅሬታ...

የለማ መገርሳ ድምፅ በኦ ቢ ኤን ቲቪ እንዳይተላለፍ መከልከሉ በሠራተኞች ዘንድ ቅሬታ ፈጠረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ረቡዕ እለት አዳማ ውስጥ በተፈጸመው የታዋቂው ባለሃብት ከቢርሁሴን ቀብር ላይ ለማ መገርሳ ተገኝተው አጭር ንግግር አድርገው የነበረ ቢሆንም የመከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር በኦሮሚያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኔትዎርክ (ኦ ቢ ኤን) እንዳይውል መደረጉ በጣቢያው ሠራተኞች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል ተባለ።

በርካታ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የተገኙበትን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ከተገኙት መገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ የነበረው ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን)፤ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ድምጽ ከማስተላለፍ መቆጠቡ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ጥያቄና ቅሬታን ፈጥሯል ሲል የቢቢሲ የአማርኛ ዜና ድህረ-ገፅም በተመሳሳይ መረጃውን ለሕዝብ አድርሷል።

የለማ መገርሳን ንግግርን የያዘው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዘገባ፣ ረቡዕ ዕለት ምሳ ሰዐት ስድስት እና ሰባት ሰዐት ላይ እንደሚሰራጭ በዕለቱ የጣቢያው መርሃ ግብር ላይ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ዜናው ወደ ምሽት እንዲተላለፍ መወሰኑን የድርጅቱ ሠራተኞች መናገራቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፤ ነገር ግን በዕለቱ ምሽት 12 እና 1 ሰዐት ዜናዎች ላይ ከዘገባው የለማ ድምጽ እንዲወጣ ተደርጎ፤ የክልሉ የፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ድምጽ በማካተት እንዲተላለፍ መደረጉን አስታውቋል::

የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቱ ዳይሬክተር “የለማ መገርሳ ድምጽ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል” በሚል ምክንያት ድምጻቸው ከዘገባው ተቆርጦ እንዲወጣ መደረጉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሠራተኞች ተናግረዋል። ይህ የዳይሬክተሩ ውሳኔ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች ጋር አለመግባባትን እንደ ፈጠረ የኦቢኤን ጋዜጠኞች በመናገር ላይ ናቸው።

“ከዚህ ቀደምም የተመረጡ ሰዎች ድምጽ እና ምስል አየር ላይ እንዳይውል ክልከላ ይደረጋል” ሲል ይህ የመጀመሪያ ክስተት እንዳልሆነ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የድርጅቱ ነባር ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል::

LEAVE A REPLY