አትፈርስም አትበሉ! || በሳምሶን አስፋው

አትፈርስም አትበሉ! || በሳምሶን አስፋው

እንደ ሃብታም አጥር – እንደ ጡብ ርብራብ፤

እንደ ድንጋይ ቁልል – እንደ ሰው ሰራሽ ግንብ፤
አትፈርስም አትበሉ! መፍረስ ምን አመጣው?
የግንበኛ ቱንቢ ውሃ ልክ ያልነካው ፤
የሃገሬ ስሪቷ ፤ መለኮታዊ ነው ……፤
ታዲያ የምን መፍረስ …? መፍረስ ምን አመጣው …?

አትፈርስም አትበሉ! ኢትዮጵያን እንደ ግንብ፤
እንደ ድንጋይ ቁልል – እንደ ጡብ ርብራብ፤

እርግጥ ነው! እውነት ነው! ሃገሬ ታማለች፤
በናት ጡት ነካሾች፤ በድውይ ልጆቿ፤ ፈተና ገብታለች!
ከውስጥም ከውጭም ስንግ ተይዛለች፤ ፋታ ተነስታለች ፤

ይህ ታዲያ አዲስ አይደል! ሁሌም አብሯት አለ፤
የልጅ አሜኬላ ማጠኗ እያፈራ ሆዷ እያበቀለ፤
ከጠላቷ አብሮ ሰላሟን ሲነሳት፤
ጉያዋን ሲያደማ ጓዳዋና ሲያምሳት፤
እልቆ መሳፍርቱ ስንት ፈተና አልፋለች?
ስንት ግዜ ታማ ስንት ግዜ ድናለች ..?
ስንት ግዜስ ወድቃ ስንቴስ ተነስታለች .!

በአያቱ ጥፉ ስም – እንዳፈረ ኖሮ ፤
አሜኬላ ዘሯ – የዘር ዝሩን ቆጥሮ፤
ዛሬም ፈትኗታል – የአያት ቂሙን ቋጥሮ፤

ይህ ታዲያ አዲስ አይደል አብሯት የኖረ ነው!
ያሁኑን ፈተና ምን ልዩ አደረገው ……?
አትፈርስም ! … ፈራሽ ነች! … መባሉ ለምን ነው?

አትፈርስም አትበሉ! ሃገሬን እንደ ግንብ፤
እንደ ድንጋይ ቁልል፤ እንደ ጡብ ርብራብ፤
የግንበኛ ቱንቢ ውሃ ልክ ያልነካው፤
በሰው ያልተሰራ – በሰው የማይፈርሰው፤
የሃገሬ ስሪቷ መለኮታዊ ነው ….፤

እርግጥ ነው! እውነት ነው! ሃገሬ ታማለች…!
በነቀርሳ ልጇ፤ በድውይ ፍሬዋ፤ ጤናዋን አጥታለች ….!
ስንግ ተይዛለች …..፤
ግና! እንደ ትናቱ ዛሬም በልጆቹዋ ፈውስ ታገኘለች፤
በብሩክ ፍሬዋ ይህን ቀን ታልፋለች …፤

የአፍሪካ ብርሃን – የምስራቋ ጮራ ፤
የጥቁር ህዝብ ኩራት – የነጻነት በሯ፤
እኔን ያስቀድመኝ -የነ አትንኩኝ እናት፤
ትናት ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ ህያው ናት፤

እና! አትፈርስም አትበሉ ሃገሬን እንደ ግንብ፤
እንደ ድንጋይ ቁልል፤ እንደ ጡብ ርብራብ፤
የግንበኛ ቱንቢ ውሃ ልክ ያልነካው፤
እጅ ያልደረደረው – እጅ የማያፈርሰው ፤
መለኮታዊ ነው …! የሃገሬ ስሪቷ፤
አፍራሿን የሚያፈርስ ቅኔ ነው ፍጥረቷ፤

LEAVE A REPLY