አሜሪካ መከላከያ ‘ወደ ትግራይ አይገባም’ መባሉን መቀበሏን አስታወቀች

አሜሪካ መከላከያ ‘ወደ ትግራይ አይገባም’ መባሉን መቀበሏን አስታወቀች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአገር መከላከያ ሰራዊት ለጊዜው በተቆጣጠራቸው የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታወች ላይ ፀንቶ እንዲቆይ መታዘዙን እንደምትቀበል አሜሪካ አስታወቀች፡፡

ዋሽንግተን ጦሩ ነጻ ባወጣቸው የአፋር እና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ ታዟል መባሉን ተከትሎ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩል መግለጫ አውጥታለች፡፡

በመግለጫው ውሳኔውን እቀበላለሁ ያለች ሲሆን መንግስት አሁንም የአየር ላይ ጥቃቶችን እንዲያቆም እና ኤርትራም ኃይሎቿን እንድታስወጣ ጠይቃለች፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን ማቆም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲያበቁ ማድረግ፣ ሰብዓዊ አቅርቦቶችን መፍቀድ እና መደራደር አለባቸው ያለችም ሲሆን ግጭቱ ምንም ዐይነት ወታደራዊ መፍትሔዎች እንደሌሉት መግለጿን አል አይን ዘግቧል፡፡

የአሜሪካ መንግስት ቀደም ሲል የህወሃት ኃይሎች “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች መውጣታቸው ግጭቱን ለማስቆም እንደሚረዳ ገልጾ ነበር፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው መግለጫ የመንግስት ጦር የአፋር ክልልን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ምስራቅ አማራን ነጻ ማውጣቱንና ጦሩ ባለበት ጸንቶ እንዲቆይ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወቃል፡፡

LEAVE A REPLY