በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! 

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! 

ለዘመናት የተጣባን ኹሉንም አፍርሶ የመገንባት የተሳሳተ ጉዟችን በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል!

*በአገራችን ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ጉዞ ከቀደመ ሥርዓት ጋር የተያያዘን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ አዲስ መሠረት መጣል ኹሉንም እንደ አዲስ የመገንባት የተሳሳተ አካሄድ ዛሬም ሊታረም አልቻለም። ይህ አካሄድ ከመንግሥትና የመንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ አልፎ ዛሬ ወደ ከተማና የከተማ ቅርስ በመዛመት በአዲስ አበባ እየተከናወነ በሚገኘው የነባር መንደሮችና ሕንጻዎች ፈረሳ የከተማችንን ታሪክ እያጠፋ ነው። በተግባር እየታዩ የሚገኙት ሁኔታዎችም በግብታዊነት የቀደመውን በማጥፋት አዲስ ታሪክ የመጻፍ ሩጫ ይመስላል። ፒያሳን ጨምሮ በሌሎች ሥፍራዎችም ነባር ሕንጻዎችን ወደ ፍርስራሽነት የመቀየርና በአዲስ የመተካት ፕሮጀክት እንደ ማዕበል ሆኖ የከተማችን ገላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እንዳልነበሩ እያደረገ ቅርሶቻችንን እየበላ የብዙዎችን ሕይወት በማናወጥ ላይ ይገኛል። “አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን” በሚል አማላይ ሀሳብ የዘመናዊ ህንጻ ግንባታ፣ ከተማና ከተሜነትን ለዘመናት ያስተዋወቀችውን የፒያሳ መንደር ማፍረስ በጥንታዊ መንደርነት ከልለን ማግኘት የምንችለውን የቱሪዝም ሀብት የሚያሳጣን ከመሆኑ ባሻገር፤ የመንግሥት የተንሸዋረረ እይታና ማንአለብኝነት ያመጣው ነው ብለን እናምናለን። 

ልማት የማይጠላ፣ የሚበረታታ እና የሚደገፍ ተግባር ነው። ነገር ግን በዕቅድ፣ በውይይት እና በስሌት መሆን ይገባዋል። ነባር መንደሮች ከመፍረሳቸው በፊት በባህል ኢንዱስትሪ መርህ ተመስርተው ወደ ሚጎበኝ ስፍራ የሚቀየሩበት  አማራጮች ላይ መምከር ይገባ ነበር። አዲስ አበባ ራሷን እንጂ ኒው ዮርክ፣ ሎንዶን፣ ቦነስአይረስ፣ ቶኪዮ፣ ናይሮቢ ወይም ዱባይን መሆን አትችልም። መሆንም አይገባትም። አዲስ አበባ ለኗሪዎቿ ምቹ ለጎብኚዎቿ ደግሞ ሳቢና ማራኪ የምትሆነው ራሷን ሆና ስትገኝ ብቻ ነው። 

ፈረሳው በዚሁ ከቀጠለ የአዲስ አበባን መነሻ አሻራ ለማየት የምንቸገር ይሆናል። ታሪክና ከየት መጤነት የሚቀሩት በፎቶና በተንቀሳቃሽ ምስል ብቻ ሳይሆን በነባር ከተማነት ከልሎ በመጠበቅ ጭምር መሆኑን መንግሥት ማስተዋል ባለመቻሉ ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመ ይገኛል። የረጅም ዘመን ታሪክና ዕድሜ ያላቸው የአለማችን ታላላቅ ከተሞች በአብዛኛው መነሻቸውን የሚያሳዩ በአግባቡ የተጠበቁ መሰል ፕሮጀክቶች አሏቸውና እንደ አዲስ ማሰብ ሳያስፈልግ በቀላሉ መኮረጅ ይቻል ነበር። ይሁን እንጂ ‘የተገነባን አፍርሶ አዲስ የመገንባት’ አባዜ እንደ አገር ዛሬም ያለቀቀን ክፉ ደዌ በመሆኑ የቀደመውን አክብሮ፣ መጥፎውን በማረም፣ መልካሙን የማስቀጠል ፍላጎት በሌለው ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ለመገኘታችን ጥሩ ማሳያ ነው። መንግሥት እያፈረሰ የሚገኘው ጥንታዊ መንደሮችን እና ሕንጻዎችን ብቻ ሳይሆን ሕዝባችን ለዘመናት የገነባውን ሥነ-ልቡናዊ ትስስር ጭምር በመሆኑ  ድርጊቱ እጅግ በጣም አሳዝኖናል። 

እየፈረሰ በሚገኘው ፒያሳና አካባቢው የትኞቹ እንደ ፈረሱና እንደሚፈርሱ ባናውቅም ለዋቢነት ያህል በቅርስነት የተመዘገቡ የሐኪም ወርቅነህ መኖሪያ ቤት በ1900ዎቹ መጀመሪያ የተገነባ፤ የአዛለች ጎበና መኖሪያ በ1900 ዎቹ መጀመሪያ የተገነባ፤ የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ አግደው መኖሪያ እ.አ.አ. በ1906 የተገነባ በዚሁ አቆጣጠር ከ1916 እስከ 1964 የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሆኖ ያገለገለ፤ ብሪቲሽ ባይብል ሶሳይቲ እ.አ.አ. በ1930ዎቹ የተገነባ፤ የመሃመድ አሊ መኖሪያ በ1900ዎቹ መጀመሪያ የተገነባ፤ የሙሴ ሚናስ ኬርቤኪያን መኖሪያ እ.አ.አ. በ1915 የተገነባ፤ የማቲግ ኬቮርኮፍ መኖሪያ እ.አ.አ. በ1910ዎች የተገነባ፤ የአህመድ ሳላህ (ሻሺብ ሃይሴት) መኖሪያ በ1900 ዎች መጀመሪያ የተገነባ፤ የአልፍሬድ ኢልግ መኖሪያ እ.አ.አ. በ 1913 የተገነባ፤ የአርቲን አቫኪያን መኖሪያ በ1900 ዎቹ መጀመሪያ የተገነባ፤ የአጋፋሪ ከልሌ መኖሪያ በ20ኛው መቶ ክፍል ዘመን መጀመሪያ የተገነባ ፤ የጳውሎስ ኮርዳስ መኖሪያ እ.አ.አ. በ1934 የተገነባና ሌሎችም ብዙ መዘርዘር የሚቻል እንዳሉ ልብ ይሏል።  

በመጨረሻም የሰራውን በነጋታው የሚያፈርሰው ከተማ አስተዳደሩ የሚያባክነው የሕዝብ ገንዘብ ነውና አሁንም ቆም ብሎ በማሰብ ቅርሶቻችን ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ የቀደመ ማነንታችን መገለጫ አሻራዎቻችን ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። የቅርስ ባለስልጣን  እና የቱሪዝም ሚኒሰቴርም ድርጊቱን የመመርመርና የማረም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።  ከመቶ ዓመት በላይ ባስቆጠረ ጊዜ የጎለበተው ማኅበረሰባዊ መስተጋብራችን በተያዘው አካሄድ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ታሪክ አልባ አዲስ አበባን ታቅፈን እንዳንቀር የትኛውም አይነት ፕሮጀክት ከስሜት ይልቅ በስሌት መጀመርና መከናወን አለበት ብለን እናምናለን። መንግሥት በዚህ ረገድ እየተከተለ ያለውን ጎዳና ቆም ብሎ በጥንቃቄ እንዲመረመርና የተገነባውን በማፍረስ ታሪክና ሀብት የማጥፋት ዘመቻውን በአስቸኳይ እንዲያቆም ታሪካዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ እና ሕዝቧን ይጠብቅ!

እናት ፓርቲ 

መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY